Sonntag, 21. Dezember 2014
Diabetes Diet & Food Tips: የስኳር ሕመምን በመከላከል ተግባር የእርስዎና የአመጋገብዎ ሚና
Posted by tenadam on January 5, 2014
ከእንግዳወርቅ ባዬ
በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን እየተስፋፉ ካሉ የሕመም ዓይነቶች አንዱ የስኳር በሽታ ነው። የስርጭት መጠኑም ወረርሽኝ ወደሚያስብል ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ሕመሙ በፍጥነት እያሻቀበ የሚታየው ደግሞ በበለጸጉ አገሮችና እንደ ኢትዮጵያ በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ነው።
ከዓለም የስኳር ሕመም ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት በዓለማችን 246 ሚሊዮን ሰዎች ከስኳር በሽታ ጋር ይኖራሉ። የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በተጠናከረ መንገድ ካልተሰራበት ይህ አሀዝ እ.አ.አ በ2025 ወደ 380 ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ ይገመታል።
በአገራችን የስኳር ሕመም ከዛሬ 30 ዓመታት በፊት አልፎ አልፎ ብቻ ይከሰት የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሚያስደነግጥ መልኩ እየተስፋፋ ለመሆኑ በየጤና ተቋማቱ በየጊዜው ለሕክምና የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ብዛት ማስረጃ ሊሆን ይችላል።
ከኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማህበር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የስኳር ሕመም የሚከሰተው ሰውነት ለኑሮም ሆነ ለእድገት የሚያስፈልገውን ስኳር በትክክል ለመጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው። በእዚህም የተነሳ አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ የስኳር ሕመም አለው ይባላል። በደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከሚፈለገው በላይ ከፍ ብሎ የሚገኘው ደግሞ ቆሽት የተባለው የሰውነት ክፍል «ኢንሱሊን» የተሰኘውን ንጥረ ነገር (በእንግሊዝኛው አጠራሩ ሆርሞን) በበቂ ሁኔታ ወይም ደግሞ ጭራሹን ማመንጨት ሲያቅተው ነው።
አንድ ሰው የስኳር ሕመም እንዳለበት በይበልጥ በደም ምርመራ ሊታወቅ ይችላል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሕመሙ አንዴ ከያዘ በባህላዊም ሆነ በሳይንሳዊ የሕክምና ዘዴ የማይድን የዕድሜ ልክ በሽታ ቢሆንም ክትትልና ቁጥጥር ከተደረገበት እንደማንኛውም ሰው ጤናማ ኑሮ ሊያስኖር ይችላል። በተገቢው መንገድ ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገበት ደግሞ የተለያዩ የጤና ጠንቆችን ለምሳሌ የዓይን፣ የኩላሊት፣ የነርቭና የልብ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል።
diabets and foodየሰውነታችን ሕዋሶች ለመተንፈስ፣ ለማየት እንዲሁም ለማሰብ ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ይህ ኃይል የሚገኘው ደግሞ ከምንበላው ምግብ ሲሆን፤ በአንጀት አማካይነት ተፈጭቶ ጉሉኮስ ወደሚባለው የስኳር ዓይነት በመለወጥ ወደ ደም ስር እንዲጓዝ ያደርጋል። ይህ ስኳር ከአንጀት ወደ ደም ይተላለፍና በደም ዝውውር አማካይነት ወደተለያዩ የሰውነት አካላት ገብቶ በኃይል ሰጪነት ያገለግላል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የስኳር ሕመም መንስኤ ምን እንደሆነ በውል አይታወቅም።ከላይ እንደተገለጸው በሽታው ቆሽት ኢንሱሊንን በሚገባ ሳያመነጭ ሲቀር የሚከሰት ነው። ምንም እንኳ በስኳር ሕመም ላይ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ጥናቶች እየተደረጉ ቢሆንም ቆሽት ኢንሱሊንን የማምረት ተግባሩን ለምን በሚገባ እንደማያካሂድ ምክንያቱ ሊታወቅ አልቻለም።
የስኳር ሕመም በእርግማን፣ በልክፍት ወይም ብዙ ጣፋጭ በመብላት የሚመጣ አይደለም። ለስኳር ሕመም መከሰት ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎች በቅርብ የቤተሰብ አባል የሕመሙ ተጠቂ መሆን (ሁልጊዜ ግን በዘር ሀረግ አይተላለፍም)፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የሕዝቡ ከገጠር ወደከተማ መፍለስ፣ጭንቀትና ውጥረት የተሞላበት ኑሮ፣ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ መከተል፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እንዲሁም የሰውነት ክብደት መጨመርና ከልክ በላይ መወፈር ይጠቀሳሉ።
ሕመሙ ዕድሜ፣ ብሔር፣ ጾታና የኑሮ ደረጃ ሳይል በሁሉም ሰው ላይ ሊከሰት ይችላል። ይሁንና ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ፣የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ የሆኑ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርጉና በቤተሰባቸው ውስጥ የስኳር ሕመም ያለባቸው፣ የደም ግፊት ያለባቸው፣በደም ውስጥ የቅባት መጠኑ (ኮሊስትሮል) ከፍ ያለባቸው ሰዎች፣ከዚህ ቀደም በእርግዝና ጊዜ የስኳር ሕመም የታየባቸውና ከዚህ ቀደም ሲል ክብደታቸው ከአራት ኪሎ ግራም በላይ የሆኑ ሕጻናትን የወለዱ ሴቶች ይበልጥ ለስኳር በሽታ የተጋለጡ ናቸው። ከእነዚህ አንዱ የታየባቸው ሰዎች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የስኳሩን መጠን ለማጣራት የደም ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በደም ውስጥ ያለው የስኳር ሕመም ሲጨምር ግልጽና የማያሻሙ ምልክቶች አሉት።አሁንም አሁንም ውሃ ውሃ ማለት፣ቶሎ ቶሎ ብዙ መሽናት፣ከፍተኛ የረሃብ ስሜት፣ድካምና ኃይል ማጣት፣ምክንያቱ ያልታወቀ የክብደት መቀነስ ምልክቶች ያሳያል። ከእነዚህ በተጨማሪ የማየት ችሎታ ለውጥ (ብዥ ማለት)፣የእግርና የእጅ መደንዘዝ፣የግብረስጋ ግንኙነት ለማድረግ አለመቻል፣ ሰውነት ሲቆስል፣ሲያብጥና ሲያሳክክ ቶሎ ያለመዳን፣ በሴቶች ላይ ማህጸን አካባቢ ማሳከክና ነጭ ፈሳሽ መውጣት፣አልፎ አልፎ የሰውነት መቆነጣጠርና ውስጥ ውስጡን የሆነ ነገር የሚሄድ ዓይነት ስሜት መሰማት ዋነኛ ምልክቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ የስኳር ሕመሞች ምንም ዓይነት የሕመም ምልክቶች አያሳዩም።
የስኳር ሕመም በአራት ዓይነት ይከፈላል። የመጀመሪያው ዓይነት የስኳር ሕመም የሚከሰተው ቆሽት ኢንሱሊንን ማምረት ሲያቆም ነው። ይህ በአብዛኛው የሚከሰተው ከ30ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ላይ ሲሆን፤ በልጆችና ከተወለዱ ትንሽ ጊዜ በሆናቸው ሕጻናት ላይም ሊታይ ይችላል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሕመሙ ሲከሰት ድንገተኛና ፈጣን ሂደት ይኖረዋል። ይህ ዓይነቱ የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች በሕይወት ለመቆየት በየቀኑ የኢንሱሊን መርፌ መወጋት ይኖርባቸዋል። በእዚህ በሽታ የተያዙት ሰዎች ከጠቅላላው የስኳር ሕሙማን ቁጥር ከ10እስከ 15 በመቶ ያህሉን ይይዛሉ።
ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ሕመም የሚከሰተው ቆሽት የሚያመርተው ኢንሱሊን በቂ ሳይሆን ወይም በደንብ የማይሰራ በሚሆንበት ጊዜ ነው።ከ85 አስከ 90 በመቶ የሚጠጉ የስኳር ሕሙማን የሁለተኛው ዓይነት የስኳር ታማሚዎች ሲሆኑ ሕመሙ ያለባቸው አብዛኞቹ ሰዎች ሁኔታውን በሚመለከት ምርመራ አድርገው የማያውቁ ናቸው።የሁለተኛው የስኳር ዓይነት ያለባቸው አብዛኛው ሰዎች ከ40 ዓመት በላይ ያሉ ሲሆኑ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸውና የአካል ብቃት አንቅስቃሴም አያደርጉም።የእዚህ የስኳር በሽታ ታማሚዎች እድሜያቸው እየጨመረ ሲመጣ ኢንሱሊንን ወደሚወስዱበት ደረጃ ይደርሳሉ።
ሦስተኛው ዓይነት የስኳር ሕመም ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሲሆን፤ የሚታየውም በእርግዝና ወቅት ብቻ ነው። እርግዝና ነክ የስኳር ሕመም ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው እርግዝና ከጀመረ ከ24እስከ 28ሳምንት በኋላ ነው። ይህ ዓይነቱ የስኳር ሕመም ከእርግዝና በኋላ የሚጠፋ ሲሆን በአንዳንድ ሴቶች ላይ ግን ከወሊድ በኋላም ሊቀጥል ይችላል። ከወሊድ በኋላ የስኳር ሕመም ቢጠፋም ወደፊት በእርግዝና ጊዜም ሆነ ከእርግዝና ውጪ ሊከሰት ስለሚችል ይህ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሴቶች ለስኳር ሕመም ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አራተኛው ዓይነት የስኳር ሕመም በሌሎች በሽታዎች ወይም በመድኃኒቶች ሳቢያ የሚከሰት የስኳር ሕመም ዓይነት ሲሆን የሚከሰተው አልፎ አልፎ ነው።
የስኳር በሽታን በሚፈለገው መንገድ ለመቆጣጠር ከተፈለገ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ወደ ትክክለኛው ማምጣት ያስፈልጋል። ይህም በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ከ90 እስከ 130 ሚሊግራም (ዲሲ ሊትር) መካከል እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። የስኳር ሕመምን በመቆጣጠር ረገድ የስኳር በሽተኛው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ግለሰቡ የሕክምና ክትትል በሚያደርግለት ዶክተርና ሌሎች የጤና ባለሙያዎች እርዳታ በመታገዝ ራሱን እንዴት መንከባከብና ሕመሙን ዕለት በዕለት እንዴት መቆጣጠር እንደሚችል መማር ይኖርበታል።
በሽታውን ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል ሲሆን፤ ለስኳር ሕመም ሕክምና የምግብ ቁጥጥር ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል። የስኳር ሕመምተኛ ምግብ ተብሎ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጥ ዝርዝር ወይም ለስኳር ሕሙማን ሁሉ የሚስማማ በሚል አንድ ወጥ መመሪያ ሊሰጥ ይችላል። ምክንያቱም ምግብና መጠጥ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ይጨምራልና። በመሆኑም ምግብ ሲመረጥ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እንዳያበዛው ወይንም እንዳይቀንሰው መጠንቀቅ ተገቢ መሆኑን ሕሙማን ሊያጤኑት ይገባል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ይቀንሳል።ለስኳር በሽተኛ ደግሞ የተለየ ጠቀሜታ አለው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትሮ ማድረግ በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር ከመርዳቱም በላይ የሰውነት ክብደት እንዳይጨምርም ያግዛል። እንቅስቃሴ በሚደረግበት ጊዜ ሰውነት በደም ውስጥ ያለውን ስኳር በፈጣን ሁኔታ ይጠቀምበታል። በመሆኑም ሁሉንም ዓይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች (የእግር ጉዞ፣የቤት ውስጥ ሥራዎች፣አትክልት መኮትኮትና ሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ) ማድረግን ያካትታል።
መድኃኒት መውሰድ በሽታውን ለመቆጣጠር ሌላው አማራጭ ነው። መድኃኒቶች በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቀነስ ይችላሉ። ለአንደኛው ዓይነት የስኳር ሕመም ኢንሱሊን በመርፌ የሚወሰድበት ምክንያት ኢንሱሊን ፕሮቲን በመሆኑ በአፍ ከተወሰደ ምግብን ለመፍጨት የሚያገለግሉ ፈሳሾች ይዘቱን ስለሚያጠፉት ነው። ኢንሱሊን መቼና በምን ያህል መጠን በየቀኑ እንደሚወሰድ ባለሙያው ይወስናል። ጠቀሜታው ጤናማ የሆነ ቆሽት የሚሰራውን ሥራ በተቻለ መጠን በመኮረጅ መስራት ነው።
ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ሕመም ምግብን አስተካክሎ በመውሰድና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ አማካይነት በደም ውስጥ ያለውን መጠን ለመቀነስ ካልተቻለ በሦስት መንገድ ሊሰሩ የሚችሉ እንክብሎች በሐኪም ሊታዘዝ ይችላል። መድኃኒቶቹ ቆሽት ብዙ ኢንሱሊንን እንዲያመርት ሊያነቃቁት ይችላሉ። ወይንም ሰውነት ያመረተው ኢንሱሊን በተሻለ መንገድ እንዲሰራ የሚያደርጉ አሊያም የምግብ መፈጨት ሂደትን ሊያዘገዩ ይችላሉ።
ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ሕመም ያለባቸው ሰዎች የሚወስዱት እንክብሎች፣ የምግብ ቁጥጥር ወይም የሚያደርጉት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ተቀባይነት ወዳለው መጠን ለማውረድ ካልቻለ ኢንሱሊንን መጀመር አስፈላጊ ሊሆንባቸው ይችላል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ተማሪዎች ለመምህራን፣ሠራተኞች ለቅርብ የሥራ ባልደረ ቦቻቸው የስኳር ሕመም እንዳለባቸው ቢያሳውቁ ይመረጣል። የሚወስዱትን የመድኃኒት ዓይነትና መጠን የሚገልጽ መታወቂያ መያዝም በአጋጣሚ ሕሊናውን ለሚስት ሰው አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለመስጠት ያስችላል።
እንክብልም ሆነ ኢንሱሊን የሚወስድ ሕመምተኛ ሁልጊዜም ቢሆን ስኳር ወይም ከረሜላ መያዝ ይኖርበታል።የስኳር መጠን ማነስ ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሲሰሙ በቶሎ ራስን ለመርዳት ይህ የራሱ ጠቀሜታ አለው።አንድ የስኳር ሕመምተኛ በተደጋጋሚ የስኳር ማነስ ምልክቶች ከተሰማው የሚወስደውን የመድኃኒት መጠን ማስተካከል ሊያስፈልግ ስለሚችል የሕክምና ክትተል የሚያደርግለትን ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
Abonnieren
Kommentare zum Post (Atom)
Keine Kommentare:
Kommentar veröffentlichen